03/07/2025
የደብረ ብርሃን ከተማ የባህል ቡድን ተቋቁሞ በቦርዱ ጸደቀ፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ ምክትል ከንቲባ የተከበሩ ወርቃለማሁ ኮስትሬ በመርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት ደብረ ብርሃንና አካባቢው በኪነጥበብ ዘርፍ የገዘፈ ታሪክ ያለውና የመካከለኛ ዘመን ስልጣኔ መነሻ እንደኾነ አስታውሰዋል፡፡
የዘርፉን ልማት ወደ ነበረበት ከፍታው ለመመለስ የደብረ ብርሃን ከተማ የባህል ቡድን መቋቋሙ ትልቅ የስኬት መጀመሪያ እንደኾነም ነው የተናገሩት።
በቁጭት የባህል ቡድን ለማቋቋም ከታቀደ ዓመታት መቆጠራቸውን አንስተው ዛሬ እውን በመኾኑ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ለዚህ እንዲበቃ ላስተባበሩና ለሰሩ የባህል ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ወደ ስራ ሲገባ ብዙ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሙ ታሳቢ በማድረግዳ የችግሩ የመፍትሄ አካል በመኾን የቡድኑ አባላት ሥራቸውን መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ ባህል ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክለዮሃንስ በበኩላቸው ከቦርዱ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ተቋማቸው 27 አባላት ያሉት የደብረ ብርሃን የባህል ቡድን ማደራጀት መቻላቸውን አብራርተዋል፡፡
የባህል ቡድኑን አርቲስት ነፃነት ዘውዴ የሚመሩት ሲሆን ነባርና ዕምቅ አቅም ያላቸው ወጣት ሙያተኞች የተካተቱበት ስለመኾኑም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሁሉ ነገር አልጋ ባልጋ ይኾናል ብሎ ከመጠበቅ ይልቅ የሚገጥማቸውን ችግር ተቋቁመው በማለፍ ዓላማቸውን ለማሳካት መዘጋጀት እንዳለባቸው ለቡድኑ አባላት መልዕክት ያስተላለፉት የደብረ ብርሃን ከተማ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ እታፈራሁ ተሰማ ናቸው፡፡
የደብረ ብርሃን አባሳደር መኾናቸውን ተገንዝበው እንቅስቃሴያቸውንና ሥራቸውን በጥንቃቄ እንዲሠሩ መክረዋል።
የባህል ቡድኑ የተቋቋመበትን ዓላማ እንዲያሳካ የሚመለከታቸው አካለት ሁሉ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ተመላክቷል፡፡