02/16/2022
Corruption regres
መንገድ ስራ ላይ እንዴት ሰርቀን በብርሃን ፍጥነት መመንደግ እንችላለን ??
*****************************
በመጀመሪያ መንገዱ ዲዛይን ሲደረግ ምክንያታዊ ያልሆኑ ግን ወጪ የሚያስወጡ ስራዎች ሊካተቱ ይችላሉ። ጥናት በሚደረግበት ጊዜ ነገሮችን አካብዶ በማቅረብ ብዙ ወጪ የሚያስወጡ ዲዛይኖች እንዲሰሩ ማድረግ። ሲገነቡም ለሌለው ነገር ስለሆነ የተደዘነው ቀለል አድርጎ በመስራት ብዙ ትርፍ ማግኘት ይቻላል።
ስራው ሲጀመር ደሞ በመጀመሪያ ለመስረቅ positionኣችን ወሳኝ ነው ... ወይም የስራ መደባችን መጠሪያ 😁😁😁 ... እንቀጥል .... ያው ኮንትራክተሩ አትራፊ ድርጅት ነው። ለማጭበርበር የማይቆፍረው ድንጋይ የለም። ስለዚህ የኮንትራክተሩን ሰራተኞች ትተን የኮንሰልታንቱን/ የአማካሪውን የማጭበርበር መንገዶች እንይ ... ከኮንሰልታንት ማን ምን ሊያደርግ ይችላል??
ሰርቬየሩ በዋነኝነት የ dimensionኦችን እውነትነት ነው የሚያረጋግጠው ለእነሱም ዶክመንት ያዘጋጃል ... ከመቆፈሩ ወይም ከመሞላቱ በፊት መሬቱ በx,y,z ይሄን ያክል ነበር በኋላ ይሄን አክሏል፣የተገነቡት እስትራክቸሮች ቁመት ስፋት እርዝመታቸው ይሄን ያክላል ፣ የማንኛውም ነገር የ borrow pitም ይሁን ስፋት፣ ቁመት ፣ ርዝመትና position እሱ ነው የሚያረጋግጠው እና በራሱም ሆነ ከኮንትራክተሩ ተነጋግሮ የተመቸውን ሊሞላ ይችላል... ወይም ኮንቴው የሰጠው ስራ ላይ ሁሉ አሜን እያለ ሊፈርም ይችላል።
Right of Way Specialist - በመንገዱ መስመር ላይ የግለሰብ/የድርጅት መሬቶች ካሉ ከወረዳ፣ ከባለቤቶችና ከመንገዱ ባለቤት ጋር በመነጋገር ካሳ እንዲሰጥ ያደርጋል። ለመንገዱም ይሁን ለBorrow የሚያስፈልጉ ይዞታዎችን ያስለቅቃል።
ማቴሪያል ዲፖርትመንት (( ማቴሪያል ኢንጂነር ፣ ማቴሪያል ኢንስፔክተር ፣ ላብራቶሪ ቴክኒሺያን))
ሜቴሪያል ኢንጂነሩ ማንኛውም በመንገዱ ስራ ላይ የሚውሉ ማቴሪያሎችን ጥራት ከላይ ሆኖ ይቆጣጠራል። ከእሱ ስር ማቴሪያል ኢንስፔክተርና ላብራቶሪ ቴክኒሻኖች ሲኖሩ እነሱም የሁሉም ስራዎች ጥራት በኮንትራቱ መሠረት እየተሰራ እንደሆነ ቴስት በመውሰድ ያረጋግጣሉ። የጥራት ጉዳይ መቶ በመቶ እዚህ ዲፓርትመንት እጅ ላይ ነው ያለው።
drafts person - ስራው ከመሰራቱ በፊት drawingኦችን ይመረምራል። ለውጥም ካስፈለገው እንዲለወጥ ያዛል።
Work Inspector - የሚያረጋግጠው earthwork ሲሰራ በአግባቡ ኮምፓክት መደረጉን ፣ ውሃም በአግባቡ እንደተሠጠው ቼክ ያረጋል። ሰርቬየሩ ደሞ ዳይሜንሽኑን ቼክ ያረግለታል። ስፋት፣ ርዝመት ፣ሙሌት ምናምኑን።
Structural Inspector - እስትራክቸሮች በትክክል መሠራታቸውን ቼክ ያረጋል። ሰርቬየሩ ዳይሜንሽንና ፖዚሽኑን ቼክ ያረግለታል።
Quantity surveyor - የሙስናው ንጉስ መሆን የሚችለው ይህ ሰው ነው። payment certificate የሚያዘጋጀው አጅሬው ነው። ሌባ ከሆነ ብዙ ነገር መስራት ይችላል። የሰርቬየሮች እርዳታ በጣም ያስፈልገዋል። እንዴት ነው? ... Work እና Structural Inspectorኡ በዚህ እስቴሽን ላይ ይሄ ይሄ ስራ ተሰርቷል ይሉታል። ሰርቬየሩ ይመጣና ደሞ የተሠሩት ስራዎች dimensionኣቸው ኢሄ ነው ይለዋል። ዳይሜንሽኖቹ እውነት ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ። ሰርቬየሩና ፈጣሪ ነው የሚያውቁት። በርግጥ workም ሆነ structural ኢንስፔክተሩ እውነታውን ያውቃሉ። ተናበው ነው የሚሰሩት። እናም ሰርቬየሩ ባመጣው ቁጥሮች ክፍያው ይዘጋጃል።
.......ሌሎች ክፍያዎች ላይ ደሞ ባብዛኛው ""Series 1000"" ላይ ያሉትን ኳንቲቲ ሰርቬየሩ ራሱ ይሞላዋል። ለምሳሌ የካምፕ ፋሲሊቲ መሟላቱን ሄዶ ቼክ ያረጋል ወይም ሪፖርት ከኮንትራክተሩ ይጠይቃል ወይም ደስ ካለው ተሟልቷል ብሎ ክፍያ እንዲከፈል ያስገባዋል። የክፍያ ዶክመንቱን (payment certificate) ካዘጋጀ በኋላም ማቴሪያል ኢንጅነሩ "መንግስት ሆይ በማቴሪያል በኩል ሀሳብ አይግባህ" ብሎ የምስክርነቱን ሲፈርም ሲኒየር ሰርቬየሩም "በዚህ ዶክመንት የተጠቀሱት ስራዎች በተባለው ቦታ ላይ ተሰርተዋል መጠናቸውም ልክ ነው ... ሀሌሉያ! " ብሎ ይፈርማል። ቀጥሎም ኳንቲቲ ሰርቬየሩ "አዎ ዶክመንቱን አዘጋጅቼዋለሁ ... ደሞ በትክክል ነው የሰራሁት ... አይኔን ግንባር ያድርገው" ብሎ ይፈርማል። ማን ቀረ ? drafts person ፣ Resident Engineer (ቦስ) እና Assistant Resident Engineer (ምክትል ቦስ) "አይናችንን ግንባር ያድርገው" ብለው ይፈርማሉ ... ግንባር በግንባር!
ከስራ መደብ መጠሪያ ወሬ ስንወጣ Quantity Surveyorኡ የክፍያ ዶክመንቱን የሚያዘጋጀው በ ERA Technical Specification And Methods of Measurement For Roadworks Manual መሠረት ነው። Manualኡ የተዘጋጀው ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚሰሩ መንገዶች Specification ለማስቀመጥና ስራዎች እንዴት መለካት እንዳለባቸው ለማሳወቅ ነው። ማንዋሉ ላይ ያሉትን በሙሉ አንድ ፕሮጀክት ላይ ይተገበራሉ ማለት አይደለም። ሁሉም የመንገድ ፕሮጀክቶች ለመንገዱ የሚያስፈልገውን አንቀፅ ብቻ ይወስዳሉ ፣ አንቀፁ ለተባለው መንገድ የማይሆን ከሆነ ደሞ ሊቀይሩትም ሊሰርዙትም ይችላሉ። እናም እዚህ ማንዋል ላይ ካሉት ዝርዝር ስራዎች እንዴት ነው የሚሰረቀው የሚለውን እናያለን።
1000: General
- ኮንትራክተሩ ያልተቀጠረ ሰራተኛ ተቀጥሯል በማለት በተጨማሪም ለሰራተኞቹና ለስራው ሊያሟላቸው የሚገቡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማለትም የቤት፣ የቢሮ ፣ የክሊኒክ ፣ የውሃ ፣ የኤሌክትሪክ፣ የአፈር ላብራቶሪ ወዘተ አገልግሎቶችን በብዛትና በጥራት እንደተሟሉ አድርጎ ሪፖርት በማቅረብ።
- ኮንትራክተሩ ለተቆጣጣሪው ሊያሟላቸው የሚገቡ ቤትና እቃዎቹ፣ ቢሮና እቃዎቹ፣ የምርምር የላብራቶሪና መሳሪያዎቹ፣ መኪና እስከ ጥገናው ፣የህክምና ፣ የስልክ፣ የውሃ ፣ የኤሌክትሪክ ወዘተ አገልግሎቶች እና አገልግሎቱን የሚሰጡ ሰራተኞችን ጨምሮ በብዛትና በጥራት እንደተሟሉ አድርጎ ሪፖርት በማቅረብ።
- ጊዜያዊ የለውጥ መንገዶች (detour) ከነ የትራፊክ ምልክቶቹና የፍሳሽ ስራዎች ሳይሰሩ ተሰርቷል በማለት ወይም በማጋነን ... detour ጥገናም ከሆነ እሱኑ በማጋነን ማፍረስም ቢሆን እንደዛው ወዘተ
- መንገዱ ሲሰራ በመንገዱ ውስጥ የግለሰብ/የድርጅት መሬት ወይም ቤት በሚያጋጥምበት ጊዜ ከፍ ያለ ካሳ ለመጠየቅና ተጠቃሚ ለመሆን ከግለሰቦችና ወረዳ ሀላፊዎች ጋር በመሆን የቆረቆሸን ቤት ደህና ቤት እንደሆነ ሰነዶችን ማዘጋጀትና ትልቅ ካሳ ከመንግሥት መጠየቅ።
ባዶ በርሃ ላይ የሚሰራ መንገድ ከሆነማ በየኪሎ ሜትሩ ቤቶችን በቆርቆሮ ሰርቶ የባለቤትነት ሰነዶችን በማዘጋጀት ብዙ ሊሰራ ይችላል።
- ለሰራተኞቹ የኤችአይቪ በተጨማሪም አስፈላጊ የክሊኒክ አገልግሎቶችን እንዳቀረቡ ማስመሰል/ማጋነን፣ ለአካባቢ ጥበቃ እንደሰራ በማቅረብ ፣ ለህብረተሰቡም የተለያዩ አገልግሎቶችን እንደሰጡ ማስመሰል/ማጋነን ወዘተ..
2000: Site Clearance
- ሳይቱ ለግንባታ clear በሚደረግበት ሰአት ክሊር የተደረገውን area አጋኖ ማቅረብ ...
- በ clearing ወቅት መፍረስ ያለበት ማንኛውም structure ካለ ስራውን አጋኖ ማቅረብ
3000: Drainage Structure
- የፍሳሽ ትቦዎች ሲሰሩ ቁፏሮውን፣ ግንባታውን፣ back fill ኡንም ጭምር quality ማሳነስ ... ክፍያ ላይ ግን quantity አጋኖ ማቅረብ
- መንገዱን አቋርጠው የሚሄዱ ትቦዎች ( cross drainage ወይም culvert) በሚሰሩበት ጊዜ ቁፏሮ፣ backfill ፣ ግንባታውን ወዘተ quality ማሳነስና እንደነገሩ መስራት ... ክፍያ ላይ ያው የተዋዋልነው ተሰርቷል ማለት
- የድንጋይ ስራዎች stone pitching፣ masonry ፣ riprap ወዘተ ስራዎችን ማጋነን
- ለድልድይና ለትቦዎች ደህንነት የሚሰሩ ግንባታዎችን ማጋነን
4000: Earthworks and Material Stabilisation
- Road bed (( ወይም የመንገዱ የመጀመሪያው ንጣፍ ማለት ይቻላል)) ሲሰራ መጀመሪያ የነበረው ጥሩ ያልሆነ አፈር (unsuitable material) ተነስቶ ሌላ ተተክቷል ይባላል ((እውነት ሊሆንም ላይሆንም ይችላል)) ለዚህም ክፍያ አለው ... ቀጥሎም Road bed ለተሰራበት ይከፈላል ... የተሰራው መጠንና ካሊቲውን ፈጣሪ ያውቃል
- ሌላው የመንገዱ ትልቁና ዋናው ወጪ Cut እና Fill ነው ።
- Cut section ሲኖር የተቆረጠውን volume አጋኖ ሪፖርት ማድረግ በተጨማሪም በቀላሉ የሚቆረጥ ወይም soft excavation ሆኖ ሳለ Hard Excavation ነው ብሎ ማስገባት ... ብሩ ይጨምራላ
- Fill section ሲሆን ደሞ ያው በጥራትም ይሁን በ volume ብዙ መብላት ይቻላል። በተጨማሪ ደሞ fill ሲደረግ በ Layer ነው የሚሞላው ለምሳሌ በ25 ሳንቲም thickness ትሞላለህ ከዛ ኮምፖክት ታደርጋለህ ከዛ ክፍያ ይሰጥሃል ... ሳይት ላይ ምን ሊደረግ ይችላል መሠለህ?? ... 1 ሜትር ለመሙላት ኮንትራቱ ላይ በ25 እየተሞላ ይጠቅጠቅ ካለ 4 Layer ይኖራል ማለት ነው። 4x25 cm = 1 ሜትር ...ሳይት ላይ ግን በ2 layer ብቻ ሊሞላ ይችላል። በ50 cm ውፍረት ማለት ነው። ኮንትራክተሩ አራቴ ሰርቶ ሊያገኝ የሚገባውን በሁለት ስራ ያገኛል ማለት ነው። በዛ ላይ ከሙሉ ወጪው በግማሽ ይድናል። ለ50 ብር ስራውም 100 ይከፈለዋል።
- Borrow area ለማግኘትም የተወሰኑ ንግግሮች ይኖራሉ በመሬቱ ባለ ይዞታዎችና በመንገዱ ባለቤት መሀል
5000 : Sub Base, Road Base and Gravel Wearing Course
- እዚህም እንደላይኛው volume በማምታታት ወይም layer በመቀሸብ ... Layer ቅሸባ ከሚገመተው በላይ አዋጭ ነው
6000 - Bituminous Surfacings and Road Base
- እዚህም እንደሌሎቹ volume ና layer ቅሸባ ነው።
8000 - Structure
እዚህ ስር ያሉት masonry work , bridges, box and slab culvert, cofferdam, timber structures, structural steelwork ወዘተ ናቸው። እንደሚታወቀው እነዚህን ለመስራት የሚያስፈልጉት ማቴሪያሎች ፌሮ ፣ ሲሚንቶ ፣ aggregate ፣formwork ያስፈልጋል። excavation እና backfill ስራዎች ይኖራሉ .... በሌባ አእምሮ do the maths!
9000 - Ancillary Work
በእዚህ ስር ያሉት gabion, mattresses, kilometer የሚያመላክቱ ኮንክሪቶች ( Kilometer Post), አስፖልቱ ላይ የሚቀቡ ቀለሞች ፣ የትራፊክ ምልክቶች ፣ guardrail ፣ ከግንባታ በኋላ አካባቢውንና borrow areaውን ወደ ተፈጥሯዊው ሁኔታ ለመመለስ የሚሰሩ ማስተካከያዎችና የእፅዋት ተከላዎች ፣ አጥሮች ፣ የእግረኛ መንገዶች ፣ ለሴፍቲ ተብለው የሚሰሩ የኮንክሪትና masonry ግድግዳዎች ወዘተ ናቸው።
.........
መንገድ ስራ ላይ ማጭበርበርና ውሸት እንደ hobby ወይም ዝንባሌ ነው። ጥዋት ተነስተህ እስፖርት እንደምትሰራው ምናምን በቃ የመንገድ ስራ ሰራተኞች ወደዛ ያዘነብላሉ። በተለይም ከአዲስ አበባ የራቀ ቦታ ላይ ከሆነ ሌቦቹ እንደፈለጉ ይፈነጩብሃል። መንግስት የለም ወይ የሚያስብለኝ ከህዝቦች መሞት ይልቅ መንገድ ስራ ላይ የሚሠራውን ሳይ ነው። ተቆጣጣሪ ሆነህ ኮንትራክተሩ እንደአለቃ ይሆንብሃል። ተቆጣጣሪ ሆነህ ኮንትራክተሩን ብታማ እንዳንተው ተቆጣጣሪ ተብሎ የተሾመው አለቃህ ይገላምጥሀል ፣ ይነዘንዝሃል። ለምን ካልክ ብዙ ሴራዎችን እየሠሩ መሮህ እንድትሄድ ያደርጉሀል። ይሄንን ፅሁፍ የፃፍኩት ስርቆቱ በግልፅ እንዲታወቅና መፍትሄ እንዲሰጠው ነው። ነገሮቹ መዘርዘራቸውም ለእያንዳንዱ ችግር የራሳችሁን መፍትሄ እንድታስቡ ነው። የተሻለ መፍትሄ ካላችሁ ወዲህ በሉ ..............
#መፍትሔው ምንድነው??
1. የመንገድ ባለቤቶች የራሳቸውንም ሰራተኛ፣ ኮንሰልታንቱንም ይሁን ኮንትራክተሮችን ማመን የለባቸውም። ከዚህ ሰርክል ወጣ እያሉ ስራዎችን ቼክ ማድረግ።
2. የተለያዩ ምርምሮችን በማሰራት አዳዲስ የአሰራርና የቁጥጥር መንገዶችን መፍጠር
3. የሚያጋልጡ ግለሰቦችን ማበረታታት
4. መንገድ ስራ ላይ በአብዛኛው በሰርተፍኬት/ዲፕሎማ ነው የሚሰሩት። እነዚህም ሰዎች ስራ እናጣለን በሚል ስጋት የተባሉትን አሜን ብለው ነው የሚሰሩት። የተማረውን ማስገባት የተሻለ ነው።
5. የመንገዶች ባለቤቶች የተቆጣጣሪውንና የራሳቸውን ሰራተኞች ደሞዝ ቢጨምሩ ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ይቀንሰዋል።
ሀሳብ መስጠት ይቻላል!