14/08/2025
"ጎጃሜ ከሚገዛኝ ኢቶጵያ ትፍረስ" ተባለ
የአማራ ፋኖ በጎጃሞችን ኹኔታ በጥሞና ኹኜ ስመለከታቸው በጣም ነው የሚያሳዝኑኝ። የኢትዮጵያን ታሪክ ያላነበበ ንጹሕና ቅን አእምሮ የተሸከመ ጀግኖች እንደኾኑ ገባኝ። በነርሱ ዓይን ኢትዮጵያ ለጎጃም እናት እንጂ ጠላት አይደለችም። እሄንን ስጽፍ ጠልቻቸው ወይም አዝኜባቸው አይደለም። ወንድምነቴ አስገድዶኝ እንጂ። ያለውንና የነበረውን ነገር ግልጽ ለማድረግ ከመፈለጌ የተነሣ እንጂ። እናም ወደ ታሪኩ ስመለስ "ገበያ በወጣሽ ይሉሺን በሰማሽ" የሚባል ተረት ነበረ። ወደ ታሪክ ንባብ ገበያ ብቅ ቢሉ ምን እንደተባልን ይሰሙ ነበረ። በሌላ ወገናቸው ደግሞ ዛሬ ላይ ያሉት የጎጃም ወጣቶች በጣም አስቀኑኝ። የኢትዮጵያን ታሪክ አለማንበብ እንዴትኮ መልካም ነገር መሰላችኹ። ሾላ በድፍን እናታለም ኢቶጵያ እያሉ መኖር!!!
እነዚህ ምስኪን የጎጃም ልጆች የኢትዮጵያን ታሪክ ቢመለከቱ ኖሮ እንኳን ለአማራ ገዢነት ይቅርና ለተገዢነትም ያፍሩ ነበረ። ኢትዮጵያዊነት ራሱ ያስጠላቸው ነበረ። ከተናቀው ጎጃም ላይ ተወልደው ይህን ያኽል ያልተነካ ሞራል ከየት አገኙት? ብዬ ስመራመር ያው አሁን እንደገለጽኩት የኢትዮጵያን ታሪክ አንብበው እንዳላወቁ ያመለክታል። በመሠረቱ በጎጠኞች እጅ ተበለሻሽቶ የተጻፈው ዂሉ እንደገና ተስተካክሎ እስኪጻፍ ድረስ ማንበብም የለባቸውም።
ለመኾኑ የሚያሸማቅቀን ታሪክ ምን ይኾን? እስኪ በየምዕራፍ ገጹ እየተከታተልኩ ልጻፍላችኹ። አንዱ አንገት አስደፊ ታሪካችን እኛው ጎጃሞች ያበላሸነው ታሪክ ነው። ይኸውም የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ ነው።
ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ማለት በእምባቦ ጦርነት ጊዜ ጎጃምን አዋርደው የኼዱ ለነገ ታሪክ ግዴታ የማይሰማቸው ሰው ነበሩ። ወታደሮቹ ሳይሸነፉ "እዚህ ቦታ አካባቢ ቆሳስዬ ወድቄያለኹና መጥተኽ ማርከኝ" ብለው እርሳቸው ቀድመው ለንጉሠ ሺዋ አቤቶ ምኒልክ መልእክት የላኩ እና የተማረኩ ሰው ናቸው። ከተማረኩ በኋላ ወታደሮቻቸው ያለአዋጊ ብቻቸውን ኹለት ሰዓት ተዋግተው ያለቁበት ታሪክ እናገኛለን። በጥቅሉ ወታደርኽ ሳይሸነፍ አንተ ቀድመኽ ተላልከኽ በመማረክ ታሪክ ለማበላሸት ስትታገል መገኘት ማለት እኮ ነው። ባጭሩ የንጉሥ ተክላማኖት ነገር አሳፋሪ ታሪክ ነበር። ዓፄ ምኒልክም ከንቀታቸው የተነሣ "ጋሜው!" በማለት ይጠሯቸው እንደነበረ አለቃ ተክሌ ጽፈዋል። ጋሜ ማለት ለዓቅመ ሔዋን ያልደረሰች ሴት ማለት ነው። "ወይ ባልዘፈንሽ፣ ከዘፈንሺም ባላሳፈርሽ" እንደሚባለው በእንባቦው ጦርነት ባልገጠሙ ኑሮ መልካም ነገር ነበረ። ከገጠሙም ወዲያ ለኋላ ታሪክ ሲሉ ባላሳፈሩን ኑሮ መልካም ነበረ። ለነገሩ ይቅርታ እየጠየቅኹ የምነግራችኹ ነገር ቢኖር ለነገ ታሪክ የሚቆረቆር ጎጃሜ አይቼም ሰምቼም አላውቅም። ባለፈው ተሰማ ካሣሁን ብቻ ለታሪክ ሲጨነቅ ሰማሁ ።
ሌላው ማፈሪያ ታሪካችን ደግሞ የደጃዝማች ጎሹ እና የደጃዝማች ዘውዴ ታሪክ ነው። በነገራችን ላይ ደጃዝማች ጎሹ ማለት የንጉሥ ተክላማኖት ዓያት ናቸው። እርሳቸው አርኖ ሚሼል ዲ አባዲ እንደጻፈው፣ ገነት ዐየለ አንበሴ ወደ አማርኛ ተርጕማ እንዳሳተመችው ደጃዝማች ጎሹ ለራስ ዓሊ ዓድረው ልጃቸው ደጃዝማች ብሩን ለማስገደል ከልጃቸው ጋር ጦርነት የገጠሙ ሰው ነበሩ። በተጨማሪም አቤቶ አበጋዝ ዘብሔረ ሺዋ የጻፈው፣ ኮንቲ ሮሲኒ ያሳተመው የዘመነ መሳፍንት ዜና መዋዕል ገጽ 816 ላይ እንዲህ ይላል። "ወበምሴተ ቀዳሚት ተጓሕለውዎ ጎጃሞች ወሖሩ ኀበ ኦሮሞ እስመ ልማዶሙ ተጓሕልዎ፣ ቅድመኒ አቅተልዎ ለራስ መርዕድ በወገራ፣ ዮምኒ ኀደግዎ ለደጃዝማች ዘውዴ በከመ ልማዶሙ ---የጎጃም ሰዎች ቅዳሜ ምሽት (ማታ) ላይ ደጃዝማች ዘውዴን ሸንግለውት ወደጠላት ግንባር ወደኦሮሞ ሰራዊት ኼዱ። ጎጃሞች ሽንገላ ልማዳቸው ነውና። ቀድሞም ራስ መርዕድ የተባለውን መሪያቸውን በወገራ አስገደሉት። ዛሬም ደግሞ እንደልማዳቸው ደጃዝማች ዘውዴን ጥለውት ኮበለሉ" ማለት ነው።
አሁንም ይኸው ዜና መዋዕል ገጽ 844 ላይ "ወአዘዞሙ ራስ ይማም ለማርየ እኁሁ ወአንደዋ ሊቦ ወለዋግ ሹም ክንፉ ከመ ይኅልፉ በተንከተም ከመ ይዕቀብዎ ለደጃዝማች ማሩ ከመ ኢይዕዱ ምድረ በጌምድር። ወዐደዉ ፈለገ አባዊ ወተዐየኑ በይባባ። ወእምዝ አኀዙ ይትቃተሉ ራስ ይማም ወደጃዝማች ማሩ። ወደጃዝማች ጎሹ በዐመዳሚት። ወተድኅሉ ደጃዝማች ጎሹ ወሰራዊቱ። እስመ ልማዶሙ ለሰብአ ጎጃም ደኃል" ይላል። ትርጕሙም ራስ ይማም ወንድሙን ደጃች ማርየን፣ አንደዋ ሊቦንና ዋግ ሹም ክንፉ የተባሉትን፣ ደጃዝማች ማሩ ወደበጌምድር እንዳይሻገር ይጠባበቁት ዘንድ ፋሲል በሠራው ድልድይ አድርገው እንዲሻገሩ አዘዛቸው። የአባይን ወንዝ ተሻግረው በይባባ ከተማ ከተሙ። ከዚህ በኋላ ራስ ይማምና ደጃዝማች ማሩ ጦርነት ጀመሩ። ደጃዝማች ጎሹ ዘውዴም ዐመዳሚት ተራራ ላይ ነበረ። ደጃዝማች ጎሹና ሰራዊቲም አስቀድሞ ሽሽት ጀመሩ። የጎጃም ሰዎች መሸሽ ልማዳቸው ነውና" ማለት ነው። በሌላ ቦታ ደግሞ እኒሁ አለቃ አበጋዝ የጻፉት ብላንደል ያሳተመው ታሪከ ነገሥት ገጽ 120 ላይ ራስ ኀይሉ ዮሴዴቅ ሣልሳይ ዓፄ ኢያሱን ወደመንበረ መንግሥታቸው ለመመለስ ጎንደር በኼዱ ጊዜ ራስ ዓሊ መጣ ሲባል ሰምተው መሸሻቸውንና ጎጃሞች በጦርነት ሳይኾን ገና በወሬ በድምፅ ብቻ የሚሸሹ በማለት የመቄዶንያውን ንጉሥ እስክንድር ጥበብ ውጤት በማመሳሰል ጽፈውብናል።
ዜና እስክንድር የተባለው መጽሐፍ ስለ መቄዶኑ ንጉሥ ስለታላቁ እስክንድር ጥበበኛነት ሲጽፍ ብረቱን እንደሰው ድምፅ እንዲያወጣ አድርጎ ሠርቶ ሰባድዐት የተባሉት የአውሬና የሰው ተፈጥሮ ያለባቸው ፍጥረቶችን ወደከተማ እንዳይመጡ፣ ከታጎሩበት ዋሻም እንዳይወጡ፣ የሰው ድምፅ እያወጣ እንዲከላከልለት ከመንገዳቸው ላይ አሰቀምጦት እንደሚኖር ይተርካል። የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊው አቤቶ አበጋዝም ጎጃሞችም በጦርነት ሳይኾን ገና ድምፅ በመስማት ብቻ ሲሸሹ ይኖራሉ ብሎ ጽፏል።
እርግጥ ጎጃም ማለት ዂሉም ልጆቹ አገር አዋራጆች ነበሩ ማለት አይደለም። ጀግኖችም ነበሩበት። ለምሳሌ በጊዮርጊስ ወልደ ዓሚድ መጽሐፍ ላይ ታሪኩ ተመዝግቦ የሚገኘው ራስ ወረኛ ፋሲል ከጎጃም ጀግኖች መካከል አንዱ ነበረ። ነገር ግን አሁንም አቤቶ አበጋዝ ዘብሔረ ሺዋ በራስ ወረኛ ፋሲል ዙሪያ ሲጽፉ ፈርጣጭ ብለው ከመጻፍ አልተገቱም። የጎጃም ጠል መንፈስ የተጠናወታቸው ይመስላሉ።
እኔ የኢትዮጵያን ታሪክ ለማጥናት ፈልጌ ወደንባብ ስገባ እያገኘኹት ያለኹት እንዲህና እንዲህ ዓይነት ማፈሪያ ማፈሪያ ታሪክ ነው። ባጭር አገላለጽ አባቶቻችን ጎጃምን ገድለው አስረክበውናል። ዛሬ ላይ ከጎጃም በስተቀር ዂሉም የአማራ ምሁራን ታሪክ ዐዋቂ ነው። እና ታዲያ ይህን እያነበበ የሚኖር አማራ እንዴት ነው ጎጃምን ለመሪነት የሚቀበለው?
ለዚህ መዳኒቱ ጎጃም ሥልጣን ከፈለገ ራሱን መቻል ብቻ ነበር የነበረበት። አለበለዚያ አንገቱን ደፍቶ መኖር ነው። ለነገሩ እንገንጠል ቢባልስ የአባቶቻችን ልጆች ስለኾንን ይህን የወንድነት ወኔ ከየት አባታችን እናመጣዋለን? ራስን መቻል እኮ ከባድ ዐላፊነት ላይ መቀመጥ ማለት ነው። ስለዚህ ከባድ ወንድነትን ይጠይቃል። እና ጎጃም ነው ለዚህ ትልቅ ነገር ዝግጁ ኹኖ የሚገኘው? ይከብዳል።