27/11/2025
+ የካህን ጡረታ የለውም +
ከልጅነታችን ጀምሮ በቤተ መቅደስ ያሳደጉን ድንቅ ድንቅ አባቶች ዛሬ ትዝ አሉኝ፡፡ ግርማ ሞገሳቸው ቅኔ ማሕሌቱን የሚሞላ ፣ መንበሩን ለማየት እስኪያስቸግር ድረስ ማዕጠንታቸው ደመና የሚሠራ ፣ ኪዳን ሲያደርሱ ፍርሃታቸው ፍርሃት የሚያጋባ ፣ እግዚኦታቸው ልብ የሚሰነጥቅ ፣ ዳዊታቸው አጋንንት የሚያርድ አባቶቼን ዛሬ አሰብኳቸው፡፡
ክህነት ማላገጫ በሆነበት በዚህ ዘመን ላይ ሆኜ ፣ የቅትለተ ዘካርያስን ዋዜማ እያየሁ አደግድገው ግብረ ሕማማት አንብበው የሚሰግዱትን ፣ የክት ልብሳቸው መቀደሻ የሆነላቸውን ፣ ሰዓታት ቆመው ፣ ማሕሌት ቆመው ፣ ዞረው አጥነው ፣ ክርስትና አንሥተው ፣ ፍትሐት ፈትተው ፣ በሽተኛ ጠይቀው ፣ የተጣላ አስታርቀው ፣ ሌሊቱን ቆመው አድረው ቀኑን ክርትት ሲሉ የሚውሉትን አባቶች ዛሬ አሰብኳቸው፡፡
አባ መቃርስ ስለ አባ ጳውሊ ሊተርክ ሲጀምር ‘መነኩሴ አይደለሁም ፤ መነኩሴ ግን አይቼ አውቃለሁ’ ብሎ ነበር፡፡ እኔም ዛሬ ልበል ‘አባት አይደለሁም አባቶችን ግን አይቼ አውቃለው’
መስቀላቸው በትልቅ ሰበን የተሸፈነች ፣ ሲያሳልሙ በውድ መዓዛ የሚያውድ መስቀል ያላቸው ፣ ጥምጥማቸው የደመና ክምር የመሰለ ፣ ጥና ይዘው ሲዞሩ መሬት የሚረግጡ የማይመስሉ ፣ መንበሩ ፊት ሲቆሙ የሚብረከረኩ ፣ ሥርዓት የሚጠነቅቁ ፣ እንደ ፀሐይ የሚያንጸባርቁ ፣ ጭራቸው ከሽበታቸው ጋር ቀለሙ አንድ የሆነ አባቶቼ አስቤ ትካዜ ውስጥ ገባሁ፡፡
ከቤተ እግዚአብሔር ውጪ መሔጃ የላቸውም ፤ ተረኛ ባይሆኑም ከመቅደሱ አይለዩም፡፡ ዕረፍት ቢሠጣቸው ከደጁ ርቀው ዕረፍት የላቸውም፡፡ የመጣ የሔደው የሚያዝዛቸው ፣ ብዙ እንዳላገለገሉ ሁሉ አጎንብሰው የሚታዘዙ የቤተ መቅደሱ አእማድ ካህናትን አሰብኳቸው፡፡
ቄስ ሀብቱ ዛሬ ትዝ አሉኝ፡፡ ጥምጥም ተሳክቶላቸው አያውቅም፡፡ የሚጠመጥሙት ደግሞ ቢጫ ጥምጥም ነበር፡፡ አጠማጠሙ ግን አይሆንላቸውም፡፡ ልጆች ነበርንና ስናያቸው ፈገግ እንላለን፡፡ ቅዳሴ ይወዳሉ፡፡ ሰሞነኛ ሆነውም ሳይሆኑም ለራሳቸውም ለሌላውም እሺ ብለው ይቀድሳሉ፡፡ ዛሬ ግን ያነሣኋቸው የንስሐ ልጆቻቸው ትዝ ብለውኝ ነው፡፡
የቄስ ሀብቱ የንስሐ ልጅ ለመሆን ፈልገህ ሔደህ ብትጠይቃቸው እሺ አይሉህም፡፡ እርሳቸው የሚቀበሉት የንስሐ ልጅ እስረኛ የሆነ ብቻ ነው፡፡ የትኛውም ወህኒ ቤት ያሉ እስረኞች የእርሳቸው ልጆች ናቸው፡፡ ለዕድሜ ልክ ወይም ለብዙ ዓመታት የታሰሩ አለዚያም ፍርድ የሚጠባበቁ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የቄስ ሀብቱ ልጆች ናቸው፡፡
ወህኒ ቤቶች ለእርሳቸው ወለል ብለው ይከፈታሉ፡፡ ጥበቃዎች በአክብሮት ያስገቧቸዋል፡፡ እየዞሩ እስረኞቹን አሳልመው ፣ ጸሎት አድርገው ፣ ንስሐ የሚገባ ካለ ሰምተው ፣ ጸሎተ ንስሐ ደግመው ይወጣሉ፡፡ ሥራቸው ወህኒ ቤት ብቻ አያበቃም፡፡ የእስረኞቹን ቤተሰቦች ደግሞ ዞረው ይጠይቃሉ፡፡ መልእክት ያደርሳሉ፡፡ የታመመ ቤተሰብ ካለ ይጠይቃሉ፡፡ የሞተ ካለ እስረኛውን ወክለው ቀብሩን ያስፈጽማሉ፡፡ እስረኛውም ባለበት መርዶ መስማት ካለበት ያረዳሉ፡፡ ያጽናናሉ፡፡
ሦስተኛው ሥራቸው ደግሞ ቢጫ የክላሰር ሽፋን ያላት መዝገባቸው ናት፡፡ በዚያ መዝገብ ላይ የእስረኞቹ የፍርድ ቤት ቀጠሮ አለ፡፡ ቀኑ ሲደርስ ባለ ቢጫ ጥምጥሙ ቄስ ሀብቱ እስረኛውን ተከትለው ችሎት ላይ ይታደማሉ፡፡ ሙሉ ቀን ከወህኒ ቤት ፍርድ ቤት ፤ ከፍርድ ቤት የእስረኛ ቤተሰብ ጋር ሲንከራተቱ ይውሉና ማታ ሰዓታት ይቆማሉ፡፡ ጠዋት ቅዳሴ ይቀድሳሉ፡፡ እኛ ደግሞ ተስተካክላ ያልተጠመጠመች ጥምጥማቸውን እያየን እንሳሳቃለን፡፡ ቄስ ሀብቱ ያረፉ ቀን ቀብራቸው ላይ ሁሉም ሰው የሚያለቅሰው ‘አባቴ አባቴ’ እያለ ነበር፡፡ የሥጋ ልጆቻቸውን ለይቶ ማወቅ አይቻልም ነበር፡፡
ዛሬ ወርቆቹ ጸሎተኛ አባቶች ትዝ አሉኝ፡፡ ‘ተዘከር’ ሲሉ ምነው ሞቼ በተጠራሁ የሚያሰኙት ምስኪን ካህናት ፣ ከቤተ መቅደስ ውጪ ሕይወት የሌላቸው እነዚያ የመቅደስ መብራቶች ትዝ አሉኝ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ገባን ብለን ስንነግራቸው የወለዱት ልጅ ያህል የፈነደቁ ፣ በሰበብ በአስባቡ ‘ክህነትህን ይባርክ’ ብለው ያሳደጉን አባቶችን አሰብኳቸው፡፡ ትንሽ ሳንቲም ማግኘት ስንጀምር ምን ላድርግልዎ ስንላቸው ጥያቄያቸው ከመስቀልና ከዳዊት ከፍ ቢል ከካባ የማያልፈውን አባቶች ዛሬ አሰብኳቸው፡፡
መጋቤ ሃይማኖት ገብረ ማርያም የመጽሐፍ መምህር ናቸው፡፡ ቤተልሔም ገብቶ እርሳቸውን ሳያገኝ የሚወጣ የለም፡፡ ጸሎት አያስታጉሉም፡፡ ጸሎት ሲጨርሱ ስንክሳር ያነባሉ፡፡ ከዚያ ትርጓሜ ወንጌል ያነባሉ፡፡ አንድ ጊዜ መጽሐፈ ሄኖክ ትርጓሜ ሲታተም ደስ ላሰኛቸው ብዬ ገዛሁላቸው፡፡ ስሠጣቸው ደስ ይላቸዋል ብዬ ነበር፡፡ ክው አሉ፡፡ ‘መጽሐፈ ሄኖክ ተተረጎመ?’ አሉኝ፡፡ አዎ አልኩኝ፡፡ ‘ዓለም ሊያልፍ ነው ማለት ነው’ አሉና ተከዙ፡፡ በጊዜው በጣም አሳቀኝ፡፡ ለምን እንኳን ብዬ አልጠየቅኳቸውም፡፡
በኋላ ግን መጽሐፈ ሄኖክ እና የዮሐንስ ራእይ ያላቸውን ትሥሥር ፣ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የዮሐንስ ራእይ ከመጽሐፈ ሄኖክ የተቀዳ ነው እስከማለት ያስደፈራቸውን የነገረ ምጽአት እውነታዎች ሳይ የየኔታ ገብረ ማርያም ድንጋጤ ተራ ነገር እንዳልሆነ እየገባኝ መጣ፡፡
መምህር ገብረ ማርያም ስብከተ ወንጌል ላይ ያገለግሉ ነበር፡፡ በኋላ ሹማምንት ሲቀያየሩ ከስብከተ ወንጌል መደበኛ ሥራ አገዷቸው፡፡ ማስተማር ሕይወታቸው ስለሆነ ቅዳሜ ቅዳሜ አድንኑ ከተባለ በኋላ ሕዝብ እስኪበተን ድረስ ያስተምሩ ነበር፡፡ ከመቅደሱ መለየት አይፈልጉም ነበር፡፡ ድንገት አንዱ መጥቶ እንዳያስተምሩ አገዳቸው፡፡ አዝነው ከቤት ታመው ቆዩ፡፡ ወር ሳይሞላ ዐረፉ፡፡
ይህ የብዙ አረጋውያን ካህናት ታሪክ ነው፡፡ በዕድሜ ብዛት ቢደክሙ ዕረፍት እንዲያደርጉ ተፈቅዶ እስኪያልፉ ድረስ ቤተ ክርስቲያን ልትጦራቸው ይገባል:: ከዚያ ውጪ ግን ካህን በጡረታ ተገለለ የሚባል ነገር የለም:: የካህን ጡረታ የለውም፡፡ የማያንቀሳቅስ ደዌ ካልያዛቸውና የአልጋ ቁራኛ ካልሆኑ በቀር ካህን አረጀ ተብሎ ከመቅደሱ ሊገለል አይገባም፡፡
ሕይወቱን ሙሉ በእግዚአብሔር ቤት የደከመ ካህን እንዴት በመጨረሻ ዓመታቱ እንደማይጠቅም ይተዋል? ንዋያተ ቅድሳት ቢሰበሩ አክብራ የምታስቀምጥ ቤተ ክርስቲያን የከበረው ካህንዋን ተሰበረ ብላ ልትጥል ትችላለችን? ከመንግሥት ሥራ በጡረታ የተገለሉ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣሉ:: ከቤተ ክርስቲያን ጡረታ ውጡ የተባሉ አባቶች ወዴት ሊሔዱ ይችላሉ? እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ "እግዚኦ ኀበ መኑ ነሐውር:: እንዘ ቃለ ሕይወት ዘለዓለም ብከ" "ጌታ ሆይ ወደ ማን እንሔዳለን? አንተ የዘለዓለም ሕይወት ቃል አለህ" ይሉ የለምን? (ዮሐ. 6:65)
ካህንና ወይን አንድ ናቸው፡፡ ዕድሜው ሲጨምር ብስለቱ ፣ እርጋታው ፣ ጥበቡና መንፈሳዊነቱ ይጨምራል፡፡ እንዴት ሰባ ዓመት የቆየ ወይን እንደ ውኃ ይደፋል? ሲቀድስ ፣ ሲያወድስ ፣ ሰዓታት ማሕሌት ሲቆም ፣ ክርስትና ሲያነሣ ፣ ፍትሐት ሲፈታ ፣ ዳዊት ሲደግም የኖረ ካህን እንዴት አረጀ ይባላል? ለመቅደሱ ግርማ ሞገስ ፣ ለደጀ ሰላሙ አክሊል የሆነ አረጋዊ ከተገኘ ካባ እንጂ ጡረታ እንዴት ይገባዋል?
ቅዱስ ጳውሎስ "ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝ" እንዳለ ካህናትም ኃይላቸው እንደ ንስር የሚታደሰው ሲደክሙና ሲያረጁ ነው::
የጸሎት ጡረታ ፣ የአገልግሎት ዕረፍት የለም፡፡ ሕይወታቸው ቤተ ክርስቲያን ናትና ‘ይበቃችኋል አትምጡ’ ሲባሉ የመኖር ትርጉም ጠፍቶባቸው ወዲያውኑ ይሞታሉ፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ መርገም ያመጣል፡፡ በየአድባራቱ ያሉ አረጋውያን ካህናት የደብሩ እጅግ ውድ ቅርስ ናቸው፡፡ የታሪክ መዝገቦች ፣ የጸሎት ምዕራጎች ፣ የስብሐተ እግዚአብሔር መሰላሎች ናቸው፡፡ እነዚህ አረጋውያን ካህናት የቀረቻቸውን ጥቂት ዕድሜ ደሞዛቸው ሳይጓደል ፣ ጥቅማቸው ሳይነካ እንደተከበሩ እየባረኩ እየጸለዩ ዳዊት እየደገሙ ቢቆዩ ለቤተ ክርስቲያን ክብር ናቸው፡፡ ጉልበት ስመን ፣ መርቀውን ቢሔዱ የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ የሽበት ዘውድ ለደፉ አረጋውያን ካህናት ካልሆነ ለማን ይሆናል?
እስከ መጨረሻይቱ ሕቅታ ድረስ ያልተቋረጠ ጸሎታቸው እንዳያልፈን ፤ መርቀውን እንዲሔዱ ፣ እንደ ይስሐቅ በረከታቸውን ፣ እንደ ያዕቆብ የእጅ መስቀላቸውን ፣ እንደ ኤልያስ መጎናጸፊያቸውን እንዲሠጡን ልንሻማ ይገባናል፡፡
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ኅዳር 2018 ዓ.ም.