16/03/2026
የተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅን ታሪካዊ ዝና የሚያድስ የ500 ካሬ ሜትር ህንፃ ግንባታ ውል ተፈረመ ።
🇪🇹መጋቢት07/2018 ዓ.ም🇪🇹
የቀድሞ የተፈሪ መኮንን ተማሪዎች ማህበር (Alumni) ለተቋሙ እድገት እያበረከተ ያለውን ታላቅ አስተዋጽኦ በማጠናከር፣ በዛሬው ዕለት የጂ+3 (G+3) ህንፃ እና የአንፊ ቲያትር ግንባታ ውል ስምምነት ከሚሼል ኮንስትራክሽን ጋር በይፋ ተፈራረመ።
በ500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፈውና ከጀርባው ለብቻው የሚቆም ዘመናዊ አንፊ ቲያትር (Amphi-theater) የሚያካትተው ይህ ፕሮጀክት፣ የኮሌጁን ጥንታዊና ታሪካዊ ይዘት በጠበቀ መልኩ እንደሚገነባ ተገልጿል። ግንባታው በ18 ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት በአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ የውጤት ተኮር ተቋማት ልማት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማ፣ ማህበሩ እያከናወነ ያለው ስራ ለሌሎች ቴክኒክና ሙያ ተቋማት አርአያ የሚሆን መሆኑን ገልጸዋል። "ማህበሩ ከዚህ በላይ ሰፊ አቅም ያለው በመሆኑ በቀጣይም ብዙ ይጠበቅበታል" ሲሉም አክለዋል።
የኮሌጁ ዋና ዲን አቶ ተሾመ ፈይሳ በመክፈቻ ንግግራቸው የቀድሞ የተፈሪ መኮንን ተማሪዎች ማህበር ለኮሌጁ እያደረገ ያለውን የላቀ ድጋፍ አድንቀዋል። ማህበሩ ለተቋሙ እድገት የቆመ ትልቅ አጋር መሆኑን በመጥቀስ በኮሌጁ ስም ጥልቅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የግንባታ ውሉን የቀድሞ የተፈሪ መኮንን ተማሪዎች ማህበር የካንትሪ ዳይሬክተርና የቦርድ ሴክሬተሪ ወ/ሮ ቆንጂት ተድላ እና የሚሼል ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ነጋዳር አበሞ በጋራ ፈርመዋል። ማህበሩ በስራና ክህሎት ቢሮ በኩል ለሚደረግለት ድጋፍ ምስጋና አቅርቦ፣ በቀጣይም የተለያዩ የአልሙናይ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን እቅድ እንዳለው ጠቁሟል።
ከህንፃ ግንባታው ጎን ለጎን የኮሌጁን የመቶ ዓመት ታሪክ ለትውልድ ለማቆየት የታሪክ መጽሐፍ የማጻፍ ስራ በይፋ ተጀምሯል። ጨረታውን ያሸነፉት የታሪክ መምህሩ ዶክተር አጉቾ አማረ ጥናቱን እንዲያካሂዱ የተለዩ ሲሆን፣ ለስራው መሳካት ኮሌጁ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ በማህበሩ ቀርቧል።
በመጨረሻም በኮሌጁ እና በቀድሞ ተማሪዎች ማህበር መካከል ያለውን አጋርነት ይበልጥ የሚያጠናክር የመግባቢያ ስምምነት (MoU) ተፈርሞ ፕሮጀክቱ በይፋ ተጀምሯል።
መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት ማሰፈንጠሪያውን ይጫኑ!
https://vm.tiktok.com
https://t.me/EntotoPtc1917
https://youtube.com/
https://www.facebook.com
ከኮሚኒኬሽን ቡድን