24/06/2022
በምዕራብ ወለጋ ከተፈፀመው ጭፍጨፋ ጋር የተያያዙ አዳዲስ መረጃዎች ይፋ ተደረጉ
ሰኔ 17/2014 ዓ.ም
ንሥር ብሮድካስት
የአማራ ማህበር በአሜሪካ ባለፈው ቅዳሜ በምእራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ አዳዲስ መረጃዎችን ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህ መሰረት አንዳንድ ተቋማት በጥቃቱ የተገደሉት በሺህ የሚቆጠሩ መሆናቸውን መግለፃቸው እንዳለ ሆኖ እስካሁን ድረስ 503 ሰዎች መገደላቸውን እንዳረጋገጠና ከእነዚህ ውስጥ የ282 ሟቾች ስም ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
ይህ ጥቃት በእለተ ቅዳሜ ከጠዋቱ 2 ሰአት አንስቶ እስከ ቀትር 11 ሰአት የቆየና 9 ሰአታትን የፈጀ እንደነበርም አስረድቷል፡፡
ሰዎችን ለመግደል ከባድ መሳሪያና ስለት ጭምር ጥቅም ላይ መዋሉን ከእማኞች ለመረዳት መቻሉን ያስታወቀው የማህበሩ መግለጫ ታጣቂዎቹ በመጀመሪያ በጦር መሳሪያ ጥቃቱን ከፈፀሙ በኋላ በመሳሪያው ህይወታቸው ያላለፈውን እየመረጡ በስለት ወግተው እንደገደሏቸውም አብራርቷል፡፡
‹‹እማኞች እንደተናገሩት በጥቃቱ ኢላማ የተደረጉት አማራዎች ሲሆኑ የሞቱት በሙሉም አማራዎች ናቸው›› ያለው መግለጫው በገና በተባለው ሰፈር ዘጠና ሁለት አስከሬኖች የተለቀሙ ቢሆንም በፀጥታ ስጋት አሁንም መሬት ላይ አስከሬኖች ወድቀው እንደሚገኙና የሟቾቹ ቁጥር እንደሚያሻቅብ መግለፃቸውን አስታውቋል፡፡
በቀበሌው አንድ መስኪድ ውስጥ 48 ሰዎች እንደተገደሉና በአካባቢው ደግሞ ሌሎች 15 አስከሬኖች በመገኘታቸው 63 ሰዎች በአንድ ላይ የተቀበሩበት ቦታ እንዳለም እማኞቹ መናገራቸውን አስረድቷል፡፡
በቀበሌው በሚገኙ ጫካዎች ውስጥ በተለያየ ቦታ በጅምላ የተቀበሩ ሰዎች እንዳሉ የጠቀሰው መግለጫው እስካሁን በተረጋገጠው መሰረት ግድያው የተፈፀመባቸውን ሰፈሮች ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህ መሰረት
በሲልሳው ሰፈር 143
በጨርቆሳ 104
በበገኔ 92
በሀያው 50
በጉቲን ሰፈር 39
በሴኒ 21
በካራቆሬ 35
በኦሮሞ ሸዋ 14
በቶሌ 5 እንዲሁም በአሶሳ ሰፈር የተገደሉት ቁጥር እስካሁን እንዳልተቆጠረ ገልጿል፡፡
በሲላው ሰፈር በሚገኘው ጃፋር መስኪድ ውስጥ ከተገደሉት 48 ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ሴቶች መሆናቸውንና ታጣቂዎቹ ከገደሏቸው በኋላ አስከሬናቸውን የማቃጠል ሙከራ አድርገው እንደነበርም ጠቅሷል፡፡
ከተገደሉት ውስጥ እድሜያቸው የገፋ አዛውንቶችና በጣም ህፃናት እንደሚገኙበት የገለፀው የአማራ ማህበር በአሜሪካ ከእነዚህ መካከል በጨርቆሴ ሰፈር ነዋሪ የሆኑት የመቶ አመት አዛውንቱ አባ ሀጂ ሁሴንና የአንድ ወር ጨቅላ የሆነው አብዱ ጀማል እንደሚገኝበት አመልክቷል፡፡
በጨፌ ሰፈር ደግሞ 60 ሴቶችና ህፃናት ብቻ መደገላቸውን አስረድቷል፡፡ አንዳንዶቹ ግድያዎች መላ ቤተሰብ ላይ የተፈፀሙ መሆናቸውን ያስረዳው መግለጫው ከእነዚህ መካከል አህመድ ዩሱፍ የተባሉት የልጅ ልጆቻቸውን ጨምሮ 31 ዘመዶቻቸው እንደተገደሉ አስታውቋል፡፡
ሼክ መሀመድ አሊ በጥቃቱ ወቅት አንድ ጫካ ውስጥ ተደብቀው ህይወታቸውን ቢያተርፉም 8 ቤተሰቦቻቸው እንደተገደሉባቸውም አመልክቷል፡፡
ማህበሩ በጥቃቱ ከተገደሉ ሰዎች መካከል የተወሰኑ የፎቶ ግራፍ ማስረጃዎችን ያካተተ ሲሆን ማንነታቸው የታወቁትን 282 ሟቾች ስም ዝርዝርም በመግለጫው አስቀምጧል።