21/04/2026
የሚመረቱ ቴክኖሎጂዎች የአከባቢን ፍላጎት መነሻ በማድረግ ለገበያዉ የማቅረብ ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥተዉ እየሰሩ እንደሚገኙ የሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ገለጹ።
ኮሌጁ የሰራዉን የፕላስቲክ ሪሳይክልና ፕሮሰስ ቴክኖሎጂን በሀዋሳ ከተማ ተደራጅቶ እየሰራ ለሚገኝ ዉበት ሀዋሳ ኢንተርፕራይዝ በ1.2 ሚሊየን ብር ግዢ በመፈጸም ርክክብ አድርጓል ።
የሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ መልካሙ በራሳ በኮሌጃቸዉ የሚመረቱ ቴክኖሎጂዎች የአከባቢን ፍላጎት መነሻ በማድረግ ችግር ፈቺ አዋጪ ቴክኖሎጂ በመስራት ለአብዢ ኢንተርፕራይዞች የማሸጋገርና በተቋም በማምረት ለገበያዉ የማቅረብ ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥተዉ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በኮሌጃቸዉ ተሰርቶ በዛሬዉ ዕለት ለርክክብ የበቃዉ ቴክኖሎጂ የፕላስቲክ ሪሳይክል ፕሮሰስ ቴክኖሎጂ መሆንና የፕላስቲክ ዉጤቶችን የሚፈጭ ፣ የሚያጥብና የሚያደርቅ ቴክኖሎጂ መሆኑን የተናገሩት የኮሌጁ ዲን የሀዋሳ ከተማ ለተጀመረዉን ስማርት ሲቲ ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆኑን ተናግረዋል።
በኮሌጁ የተመረተዉ ይህ ቴክኖሎጂ ከዉጪ የሚገቡ የቴክኖሎጂ ዉጤቶች ሊተካ የሚችል ቴክኖሎጂ መሆኑን የተናገሩት የኮሌጁ ዲን ለአከባቢ ጥበቃ አበርክቶ ሚናዉ ከፍተኛ መሆንን ተናግረዋል።
የሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ምክትል ዲንና የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢ/ኤ ዋና አስተባባሪ ወ/ሮ ከበብሽ ተሰማ ይህ የተመረተዉ ቴክኖሎጂን እሴት ሰንሰለት ትንተናን መነሻ በማድረግ የተሰራ ቴክኖሎጂ በማንፋክቸሪንግ ዲፖርትመነት የአከባቢን ብክለት ችግር መነሻ ተደርጎ የተሰራ መሆኑንና ቴክኖሎጂውን ሰርቶ ለማጠናቀቅ የሁለት ዓመት ጊዜ መዉሰዱን ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂው ሲሰራ አካል ጉዳተኞችን እና ሴቶችን ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን እንዲሁም የሚሰሩ ማንኛዉም ስራዎች ከእጅ ንኪኪ ነጻ መሆኑን ከምክትል ዲኗ ገለጻ ለመረዳት ችለናል።
የዉበት ሀዋሳ ኢንተርፕራይዝ ማናጀር አቶ አልታየ የቦ በቀላሉ ሊበሰብስ የማይችል ሀይላንድዶችን የመፍጨት የማጠብ ስራዎችን የሚሰራ ቴክኖሎጂ በመሆኑ ይህንን ቴክኖሎጂ በአግባብ በመጠቀም የማህበራቸዉን የዉስጥ ገቢያቸዉን ለማሳደግ ትልቅ አበርክቶ እንዳለዉ ተናግረዋል።