05/06/2026
13ኛው ዓለም አቀፍ የማህበራዊ ሳይንስ አመታዊ ጉባኤ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተጀመረ
ግንቦት 28/2018 ዓ.ም፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ
13ኛው በግጭትና በማህበራዊ ቀውስ ላይ ያተኮረ ዓመታዊ ዓለም አቀፍ የማህበራዊ ሳይንስ ኮንፈረንስ በደማቅ ሁኔታ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ
ተጀምሯል።
በመክፈቻ መርሃ ግብሩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ ዲን ዶ/ር አየለ ታሪኩ፣ 13ኛው ዓለም አቀፍ የማህበራዊ ሳይንስ ጉባኤ ምሁራንን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ ተግባሪዎችንና የማህበረሰብ መሪዎችን በአንድ መድረክ በማሰባሰብ በሀገሪቱ ግጭቶችና ማህበራዊ ቀውሶች ዙሪያ ዘላቂ መፍትሔዎችን ለመፈለግ ጠቃሚ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር አየለ በንግግራቸው፣ “ግጭት፣ ማህበራዊ ቀውስ እና በኢትዮጵያ ሰላማዊ ለውጥን ማሳደድ፡ መፈናቀል እና የማህበረሰብ መቋቋም” በሚል ጭብጥ የተዘጋጀው ኮንፈረንስ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ፈተናዎች በጥልቀት በምርምር ለመወያየትና በምርምር የተደገፉ መፍትሔዎችን ለማመንጨት ጠቃሚ መድረክ መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም የማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ በትምህርት፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት የላቀ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸው፣ እስከ 2030 ድረስ በኢትዮጵያ ቀዳሚ እና በምስራቅ አፍሪካ ተመራጭ የማህበራዊ ሳይንስ ምርምርና ትምህርት ማዕከል ራዕይ መሆኑን አስታውቀዋል።
በመጨረሻም በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ በመንቀሳቀስ ገደቦች፣ በሲቪል መብቶች ጥሰት፣ በመፈናቀል፣ በሴቶችና ሕፃናት ጉዳዮች እንዲሁም በማህበረሰብ የመቋቋም ልምዶች ዙሪያ ጥልቅ ውይይቶችና የምርምር ትዕይንቶች እንደሚካሄዱ ገልጸው፣ ተሳታፊዎች ውጤታማና አነቃቂ ቆይታ እንዲያደርጉ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
የመርሃግብሩን በይፋ የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ወደ ራስ-ገዝ (Autonomous) የምርምር ዩኒቨርሲቲነት በመሸጋገር ላይ ባለበት በዚህ ወሳኝ ወቅት 13ኛው ዓለም አቀፍ የማህበራዊ ሳይንስ አውደ ጥናት መካሄዱ እጅግ ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር መንገሻ በንግግራቸው፣ ኮንፈረንሱ በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ የተሰማሩ ተመራማሪዎችን፣ ምሁራንንና ፖሊሲ አውጪዎችን በአንድ መድረክ በማሰባሰብ በዘርፉ ያሉ ወቅታዊ ችግሮችና ዕድሎች ላይ ጥልቅ ምክክር ለማካሄድ ጠቃሚ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ የዲጂታል ሽግግር ጉዞ ውስጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸው፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከትምህርትና ከምርምር ባሻገር ለማህበረሰብ የመፍትሔ ምንጭና ችግር ፈቺ ተቋማት መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በመጨረሻም እንደዚህ ዓይነት አካዳሚክ መድረኮች በሀገራዊ ፈተናዎች ላይ በእውቀት የተመሰረቱ መፍትሔዎችን ለማፍለቅና በፖሊሲ ማበልጸጊያ ሂደቶች ላይ አስተዋፅኦ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኤመሬተስ ፕሮፌሰርና የኢትዮጵያ ታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ቁልፍ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ የታሪክ አረዳዳችን አንዳንድ ጊዜ ለማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ምንጭ መሆኑን በመግለጽ፣ መለያየትን ሳይሆን መተባበርን፣ መግባባትንና አብሮ መኖርን ማጠናከር ለሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም፣ የታሪክ ምሁራን ታሪክን ሲጽፉ በሀቅና በእውነታ ላይ በመመስረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበው፣ በተለይም የግጭት መንስኤዎችን በጥልቀት በመመርመር ለመፍትሄ የሚያግዙ ዕውቀቶችን ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
ፕ/ር ባህሩ በንግግራቸው፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ ውስጥ ያጋጠሟትን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ፈተናዎች ከታሪካዊ እይታ አንፃር በማብራራት፣ ዘላቂ ሰላምና ማህበራዊ መረጋጋትን ለማምጣት በውይይት፣ በምርምርና በማካተት ላይ የተመሰረተ አቀራረብ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም፣ የአካዳሚክ ተቋማት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሳይንሳዊ ማስረጃ የተደገፉ ሐሳቦችን በማቅረብና ትውልድን ለሰላማዊ አብሮነት በማዘጋጀት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ ማህበራዊ ቀውሶችን ለመቋቋም ከታሪክ የሚገኙ ትምህርቶችን በጥበብ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።
በየዘርፉ የሚገኙ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና ሌሎች ተዛማጅ አካላት በሀገራዊ ችግሮች ላይ የራሳቸውን ኃላፊነት በተገቢው ሁኔታ ሊወጡ እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል። በመጨረሻም፣ ታሪክ ትምህርት ቤት እንጂ እስር ቤት መሆን የለበትም በማለት ቁልፍ መልዕክታቸውን ፕሮፌሰር ብርሀኑ ዘውዴ አጠናቀዋል።
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ አምሳሉ በቁልፍ መልእክታቸው ኢትዮጵያ ያላትን ታሪካዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶች በምርምርና በሳይንሳዊ እይታ መገንዘብ ለሀገራዊ አንድነት፣ ለማህበራዊ መግባባትና ለዘላቂ ልማት መሠረታዊ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም፣ የከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ተቋማት ሀገራዊ ጉዳዮችን በጥልቀት በማጥናት በማስረጃ የተደገፉ ዕውቀቶችን ለፖሊሲ አውጪዎችና ለማህበረሰቡ ማቅረብ እንዳለባቸው አስገንዝበው፣ የታሪክና የባህል እሴቶችን ለትውልድ በማስተላለፍ ሰላማዊ አብሮነትን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
አክለውም “ግጭት በጋራ የሚፈጠር እንደመሆኑ ሁሉ፣ ሰላምም በጋራ መፈጠር አለበት” በማለት ዘላቂ ሰላም የሁሉንም ተሳትፎ እንደሚጠይቅ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በተጨማሪም የፖለቲካ ማሻሻያ፣ የሲቪክ መተማመን (Civic Trust)፣ የጋራ ተቋማት ግንባታና መደበኛ ውይይት ሲጣመሩ አዲስ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር መሠረት እንደሚሆኑ ገልጸዋል።እንዲሁም የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በድንበር ለውጦች፣ በልሂቃን ውሳኔዎችና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይሆን በሊቃውንትና በማህበረሰብ መካከል በሚፈጠር ጠንካራ ግንኙነት እንደሚወሰን ጠቅሰው፣ ከግጭት መባዛት ወደ ሰላም ግንባታ ለመሸጋገር የጋራ ርብርብ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
ኮንፈረንሱ በግጭት አፈታት፣ በማህበራዊ ቀውሶች፣ በሰላም ግንባታ፣ በማህበራዊ ትስስርና በዘላቂ ልማት ዙሪያ የሚያተኩሩ የምርምር ጽሑፎችን፣ የውይይት መድረኮችንና ሙያዊ የልምድ ልውውጦችን ያካተተ ሲሆን፣ ለሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ዕውቀት ልውውጥ እንዲሁም ለዘላቂ መፍትሔዎች ፍለጋ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ይታመናል።