የወ/ሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ታሪክ
የወ/ሮ ስኂን ት/ቤት በንጉሥ ሚካኤል ልጅ በወ/ሮ ስኂን ሚካኤል በ1922 ዓ.ም ሳላይሽ በሚገኘው የልጃቸው ጃንጥራር ኃ/ማርያም አስፋው ርስት ላይ በ25,000 ብር ተሠራ፡፡ ይህም በሀገራችን ዘመናዊ የትምህርት ታሪክ ከተመሰረቱት የመጀመሪያ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ ያደርገዋል፡፡ ላለፉት 89 ዓመታት በተለያዩ የዕድገት ደረጃዎች ውስጥ አልፎ አሁን ካለበት የፖሊቴክኒክነት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በነዚህ ጊዜያት በሀገር አቀፍም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሙዚቃው፣ በፖለቲካው እና ኢኮኖሚው ትልቅ ዝናን ያተረፉ ዜጎች የተገኙበት የትምህርት ተቋም ነው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ በዘመን ቅደም ተከተል የ
ቀረበው አጭር ጽሑፍ ይህንኑ ታሪክ ያሳያል፡፡
ታሪካዊ ዳራ እና እድገቱ
በ1920 ዓ.ም ወ/ሮ ስኂን ሚካኤል ከራሳቸው 25000 ማሪያ ቴሬዛ (ጠገራ ብር) እና በራሳቸው ርስት ላይ ከህልፈተ-ሕይወታቸው አስቀድመው ለልጃቸው በሰጡት ኑዛዜ መሰረት ከ2 ዓመታት በኋላ በ1922 ዓ.ም ደሴ ከተማ ሳላይሽ አካባቢ በ4 የመማሪያ ክፍሎች ተመሰረተ፤
በ1939 ዓ.ም የተማሪ ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት ቁጥራቸው በርከት ያሉ መማሪያ ክፍሎችን የያዘ አዲስ ሕንፃ ተገንብቶ አሁን ወዳለበት ዋናው (ስኂን) ግቢ ተዛወረ፡፡ በዚያን ወቅት ከ1ኛ - 8ኛ ክፍል ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተምር ነበር፡፡ አሁን ዋናው ግቢ (ስኂን ግቢ) የሚገኝበት ቦታ ላይ ትምህርት ቤቱ አንዲሰራ የመሰረት ድንጋይ የጣሉት የስኂን ሚካኤል የልጅ ልጅ አልጋወራሽ መርድ አዝማች አስፋወሰን ኃይለስላሴ ናቸው፡፡ በዚህ ወቅት 15 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ተሰሩ፡፡
በ1950 ዓ.ም ወደ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ከፍ አለ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለመስጠት የተቀበላቸው ተማሪዎች ቁጥርም 63 ደርሶ ነበር፡፡
በ1953 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ለሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና (ለሎንዶን ጂ.ሲ.ኤ. ፈተና) እንዲቀመጡ ተደረገ፡፡
በ1953 ዓ.ም እቴጌ መነን /የስኂን ሚካኤል ልጅ/ ለተለያዩ የሙያ ሥልጠናዎች የሚያገለግል ሕንፃ ቮኬሽናል ግቢ በ160,000 ብር አስገነቡ፡፡ በዚህ ወቅት በቀለም ትምህርት ዘርፍ ብቻ ተማሪዎችን ማስተማር በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ ከቀለም ትምህርት ጐን ለጐን በመምህርነት ሙያ፣ በእርሻና ተግባረዕድ ሙያወች ስልጠና መሰጠት ተጀመረ፡፡ ይህ ሁኔታ ትምህርት ቤቱን በሀገሪቱ የመጀመሪያው አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሆን አድርጐታል፡፡
1956 ዓ.ም የስኂን ት/ቤት የሙዚቃ ባንድ ተቋቋመ፡፡ ባንዱ ሲቋቋም 40 ተማሪዎች የነበሩ ሲሆን መምህሩም ሚ/ር ሮናልድ ቤል የተባለ አሜሪካዊ ነበር፡፡
በ1956 ዓ.ም የ1ዐኛ ክፍልን ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች የ2 ዓመት የሙያ ሥልጠና በተለያዩ መስኮች በመውሰድ ዲኘሎማ ማግኘት ጀመሩ፡፡ ይህ ሁኔታ እስከ 1976 ዓ.ም ቀጠለ፡፡
በ1972 ዓ.ም የት/ቤቱ ስም የካቲት 66 አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፤ ከዚያም የካቲት 66 የቀለም ቴክኒክና ሙያ ት/ቤት በሚል ተቀይሮ፣ ከዚያም የካቲት 66 የቀለም፣ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ተባለ፡፡
በ1980 ዓ.ም በ10+3 የቴክኒክና ሙያ መርሀ-ግብር ስልጠና መስጠት ጀመረ
በ1977 ዓ.ም የ1ዐኛ ክፍል ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት ያጠናቀቁ ተማሪዎች በተለያዩ የሙያ መስኮች ለ2ኛ ደረጃ ሠርቲፍኬት ሥልጠና ጀመሩ፡፡ ይህም ሁኔታ እስከ 1980 ዓ.ም ቀጠለ፡፡ ከዚህ በኋላ የሥልጠናው ጊዜ ከ2 ዓመት ወደ 3 ዓመት ከፍ አለ፡፡
በ1984 ዓ.ም የት/ቤቱ ስም ወ/ሮ ስኂን የቀለም ቴክኒክና ሙያ ት/ቤት ተብሎ ተሰየመ፡፡
በ1992 ዓ.ም ሲሰጡ ከነበሩት የሙያ ስልጠና ዓይነቶች በተጨማሪ የኮንስትራክሽን የሥልጠና ዘርፍ ተከፈተ፡፡
በ1993 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ የቴክኒክና ሙያ ተቋም ሆነ፡፡
በ1994 ዓ.ም የት/ቤቱ ስም ወ/ሮ ስኂን ቴክኒክና ሙያ ተቋም በሚል እንዲጠራ ተደርጐ በተለያዩ የሥልጠና ዘርፎች በመደበኛና በማታ መርሃ-ግብር የ1ዐ+1 እና 1ዐ+2 ሥልጠናዎች በመስጠት በሰርቲፍኬት ደረጃ ማስመረቅ ጀመረ፡፡
በ1996 ዓ.ም ተቋሙ ከደሴ ቴክኒክና ሙያ ተቋም ጋር ተቀላቀለ፡፡
በ1996 ዓ.ም ተቋሙ በጤና ኤክስቴንሽን ሙያ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ሴት ሠልጣኞችን ተቀብሎ ማሰልጠን ጀመረ፡፡
የሙያ መስኮቹም 19 ደረሱ፡፡
በ2000 ዓ.ም ተቋሙ ከደሴ ቢዝነስና ሥራ አመራር ኮሌጅ ጋር ተዋህዶ ስሙም ወ/ሮ ስኂን ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ በሚል ተቀየረ፡፡
በ2003 ዓ.ም ኮሌጁ ወደ ወ/ሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አደገ፡፡ በዚሁ ዓመትም በደረጃ 5 ስልጠና መስጠት ጀመረ፤
ስልጠና የሚሰጥባቸው ግቢዎች፡-
1. ስኂን ካምፓስ (ዋናው ግቢ)፡- ኤሌክትሪካል ኤሌክትሮኒክስ፣ ሆቴል ባህልና ቱሪዝም፣ ከተማ ግብርና እና ከተማ አገልግሎት (Urban Agriculture& Municipality)፣ እንዲሁም የጨርቃጨርቃ እና አልባሳት (Garment &Textile) ስልጠና ዘርፎች
2. ቮኬሽናል ካምፓስ (መነን ህንጻ)፡ ብረታ ብረት ምህንድስና (Metal Manufacturing & Engineering) ዘርፍ ማሰልጠኛ
3. ሆጤ ካምፓስ፡ የኮንስትራክሽን ስልጠና ዘርፎች ማሰልጠኛና የማምረቻ ማዕከል (ማምረቻ ዩኒትን) የያዘ
4. መርሆ ካምፓስ (የቀድሞ የአልጋወራሽ ቤተ-መንግስት የነበረና በኋላም ቢዝነስ እና ስራ አመራር ኮሌጅ የተመሰረተበት)፡ አሁን የInformation & Telecommunication ስልጠና ዘርፍ የሚሰጥበት፤ እንዲሁም የመርሆ ቤተ-መንግስት የሚገኝበት
5. ዳውዶ ካምፓስ (የቀድሞው SDC ተቋም)፡- የአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጅ እና የእንጨት ስራ (Furniture) ዘርፎች ማሰልጠኛ ናቸው፡፡
ኮሌጁ አሁን ያለበት ሁኔታ፡-
ከላይ እንደተገፀው ኮሌጁ በ2000 ዓ.ም ቀደም ሲል የተመሰረቱትን የወ/ሮ ስኂን ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋምን፤ የደሴ ቢዝነስና ሥራ አመራር ኮሌጅን እና የደሴ ሙያ ማሰልጠኛ ተቋምን በማዋሃድ የተደራጀ ሲሆን፤ ወደ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅነት ደረጃ ያደገው ደግሞ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኮሌጁ ያለበትን ሁኔታ ስንመለከት
ስልጠና የሚሰጠው ከደረጃ 1 እስከ 5 በ0 ዋና ዋና ስልጠና ዘርፎችና ከ56 በሚበልጡ ሙያዎች ሲሆን እያንዳንዱ ሰልጣኝ በየደረጃው ተመዝኖ ብቁ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ በ2011 በጀት ዓመት እስከ ሚያዚያ 2011 ዓ.ም ድረስ ባለው ሁኔታ 5975 የሚጠጉ ሰልጣኞችን እያሰለጠነ ይገኛል፡፡
አዳዲስ የሙያ መስኮች ከመከፈታቸው በፊት የአካባቢውን ገበያ እና ኢንዱስትሪ ፍላጎት የዳሰሳ ጥናት ይደረጋል፤
ስልጠናው ፕሮጀክትን መሰረት ያደረገ ነው፤
ከስልጠናው ጎን ለጎን ሰልጣኞች ቁጠባ እንዲቆጥቡ ይደረጋል፤ ከዚያም ቅድመ-ኢንተርፕራይዝ እንዲመሰረቱ እድል ይፈጠርላቸዋል፡፡
ከ1994 ዓ.ም (ሙሉ በሙሉ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና መስጠት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ) እስካሁን ድረስ ከ45 ሺህ በላይ ዜጎች በበርካታ የሙያ አይነቶች በቀንና በማታ ፕሮግራም ተመርቀው ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለሌሎች ስራ-አጥ ወገኖች የስራ እድል ፈጣሪ መሆን የቻሉ ዜጎችን አስመርቋል፡፡
ከምረቃ በኋላ ሰልጣኞች ያሉበትን የስራ ሁኔታ በማጥናት ድጋፍና ክትትል ያደርጋል፡፡
ለደንበኞች በሚሰጠው አገልግሎት የISO 9001:2008 ስታንዳርዶችን ያሟላ በመሆኑ በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ አማካኝነት የጥራት ስራ አመራር ማረጋገጫ በ2006 ዓ.ም አግኝቷል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ስታንዳርዱን ማስጠበቁን በኤጄንሲው በኩል ሰርቬይላንስ ኦዲት በየዓመቱ ተካሂዶ ማረጋገጫ ተሰጥቷል፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ የኮሌጁ አገልግሎት አሰጣጥ ስታንዳርዶችን ያሟላ መሆኑን ነው፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ISO 19011:2015ን አሰራርን የዘረጋ ሲሆን የማረጋገጫ ሰርቲፊኬቱን ለማግኘት በሂደት ላይ ነው፡፡
ከተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የተሻሉ ተሞክሮዎችን በማስፋት ተግባራዊ አድርጓል፡፡
የካይዘን ፍልስፍና ወደሀገራችን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉም የስልጠና ሾፖችና የስራ ክፍሎች በካይዘን እንዲደራጁ ተደርጓል፡፡
በተመሳሳይ ሌላኛውና ትልቁ ተልዕኮው ደግሞ የደንበኞቹን እና የአካባቢውን መካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪ የቴክኖሎጅ ፍላጎት መሰረት ያደረገ የምርትና ማምረቻ ቴክኖሎጅ በማላመድ እና በፈጠራ በመስራት፤ ብሎም በማሸጋገር ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችንና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ እያደረገ ነው፡፡
በተለያዩ የስራ መስኮች ለተሰማሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በአራቱም የድጋፍ ማዕቀፎች የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት በመስጠት የአሰራር፣ የክህሎት፣ የአመለካከት እና የኢኮኖሚ አቅማቸውን ከፍ ከማድረግ አልፎ ወደመካከለኛ የኢንዱስትሪነት እንዲያድጉ የሚያስችል አቅም እየፈጠረ ነው፡፡
የአሰልጣኝ መምህራንንና የአስተዳደር ሰራተኛውን አቅም ለመገንባት የረጅምና የአጭር ጊዜ ስልጠና ያመቻቻል፡፡ በተጨማሪም ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ የማሰልጠኛ ማሽኖችና ግብዓቶችን በመግዛት፣ ወርክሾፖችን በመገንባት የራሱን አቅም እየገነባ ነው፡፡
በቀጣይም በሀገር አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት የመሆን ዋነኛ ዓላማ አለው፡፡
ኮሌጁ ከዋና ዋና ተልዕኮዎቹ ጎን ለጎን በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ማህበራዊ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ ከዚህ መካከል በቅርቡ ለክፍለ-ከተሞች ከ300 በላይ የአዳራሽ ወንበሮች፣ በርካታ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩና በአዳዲስ የተተኩ ኮምፒዩተሮች፣ ለአቻ ተቋማት (ኮሌጆች) የጋርመንትና ቴክስታይል ማሽኖች እና ያገለገሉ ኮምፒዩተሮች እንዲሁም አንድ የመስክ መኪና፣ ለአረጋዊያን በየዓመቱ የተደረገ የአልባሳት ድጋፍ፣ ከተለያዩ ቦታዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ከስታፉ እና ከኮሌጁ የተደረገ የፋይናንስ እና የቁሳቁስ ድጋፍ፣ ለ5 ኅፃናት በፀረ-ኤድስ ፈንድ በየወሩ ቋሚ የገንዘብ ድጋፍ እና በየ6 ወሩ ደግሞ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ባለፉት 4 ዓመታት ብቻ የተደረጉ ድጋፎች ናቸው፡፡