05/09/2026
በዩኒቨርሲቲው የሰለጠኑ ከ300 በላይ የስቴም ማዕከል ሰልጣኞች ተመረቁ
===========***********===========
ዲ.ዩ: ነሐሴ 30/2018ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)
በዲላ ዩኒቨርሲቲ በ2018ዓ.ም በተለያዩ የሳይንስ ዘርፎች በስቴም ማዕከል የሰለጠኑ ከ300 በላይ ሰልጣኞች ተመርቀዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪ ግንኙነት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይረክተር አዲሱ ፍርንጆ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ ማዕከሉ ባጠቃላይ ከ3500 በላይ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ማስመረቁን እና የማዕከሉ ምሩቃንም ባሁኑ ጊዜ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
አክለውም በዛሬው ዕለት የተመረቁ ከ300 በላይ ተማሪዎች በክረምት፣ በሳምንቱ መጨረሻ እንዲሁም በጂኦስፖሻል ስልጠናና በተለያዩ ዘርፎች ስልጠናውን ተከታትለው ለምረቃ መብቃታቸውን ጠቁመዋል።
ማዕከሉ ጥራት ያለው ስልጠናዎችን ስለሚሰጥ፣ ባሳለፍነው ዓመት በEmerging technology በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁን ጠቁመው፣ ተማሪዎች የሳይንስ ፈጠራ እውቀታቸው እንዲጎለብት ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ አውስተዋል።
ሰልጣኞች እዚህ ያገኙትን እውቀት ወደየ ትምህርት ቤቶቻቸው ሲመለሱ ለሌሎችም እንዲያካፍሉ እና የሳይንስ ፈጣሪ ዜጎችን እንዲፈጥሩም አደራ ብለዋል። በቀጣይ ዓመት ወደ ማዕከሉ ሲመጡም አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ይዘው እንዲመጡ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ጳውሎስ በበኩላቸው፣ የጅኦስፓሻል ስልጠና በሀገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ዜጎችን ለመፍጠር ባለድርሻ አካላት ተባብረው ያዘጋጁት እንዲሁም የሚደግፉት ስልጠና መሆኑን አውስተዋል። ዲላ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ረገድ ተጽህኖ ፈጣሪ ዜጎችን እየፈጠረ እንደሚገኝ ገልፀው፣ ዩኒቨርሲቲው በትውልድ ላይ እየሰራ ላለውና እየተመዘገበ ላለው የሚጨበጥ ለውጥ በክልሉ ስም አመስግነዋል።
በተለይ በክረምቱ የተሰጠው የጂኦስፓሻል ስልጠናን በየዓመቱ ለመስጠት እቅድ ስለመኖሩ የገለፁት ኃላፊው፣ የሰለጠኑ ተማሪዎች እድሉን ላላገኙ ወንድሞቻቸው ያገኙትን እውቀት እንዲያገሩ አደራ ብለዋል።
የጌዴኦ ዞን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረጄ ሾንጣ ተመራቂ ተማሪዎችን እንኳን ለምረቃ ቀናችሁ አደረሳችሁ ብለዋቸዋል። ኃላፊው አክለውም በዚህ ጊዜ ላይ ዓለም በቴክኖሎጂ ዘርፍ ውድድር ላይ እንደምትገኝ ጠቁመው፣ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ላይ በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን በልዩ ትኩረት እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ጊዜያት ላይ እንደ ሀገር የተያዘው እቅድ ከግብ እንዲደርስ የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ አውስተዋል።
ወቅቱ ቴክኖሎጂ የየለት ስራዎቻችን ጋር የበለጠ የተቆራኘበት በመሆኑ፣ ተማሪዎች ከዚህ ሲመለሱ ማህበረሰቡ ጋር ያሉ ችግሮችን በቅርበት በመከታተል ንድፈ ሀሳብ በማዘጋጀት ችግር ፈቺ ፕሮጀክቶችን እንዲያስቡ ጥሪ ያቀረቡት ኃላፊው ዞኑ እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ አካላት ድጋፍ እንደሚያደርጉ አውስተዋል።
በመድረኩ ለ45 ቀናት በስፔስ እና ጂኦስፓሽያል ዘርፍ ላይ ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ ተማሪዎችም ተመርቀዋል። በስልጠናው ወቅት ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የእውቅና የምስክር ወረቀት እና የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
=== # # #===