27/08/2026
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሳሳካዋ አፍሪካ አሶሴሽን (Sasakawa Africa Association) ከተባለ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡
───
የመግባቢያ ሰነዱን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እና ዶ/ር ኤርምያስ አባተ የሳሳካዋ አፍሪካ አሶሴሽን (Sasakawa Africa Association) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጋራ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ህንፃ ዛሬ ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም. ተፈራርመዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በጋራ መግባቢያ ሰነድ ፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ እንደገለፁት የሳሳካዋ አፍሪካ አሶሴሽን ከዚህ ቀደም በርካታ ተግባራትን ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ሲያከናውን የቆዬ ቢሆንም ዛሬ ግን የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ወደ ራስ ገዝነት በምናደርገው ጉዞ በአቅም ግንባታ እና በተለያዩ የልማት መስኮች በአጋርነት ትውልድን የሚጠቅምና በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ የሚያደርግ ተግባራትን በጋራ እናከናውናለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
የሳሳካዋ አፍሪካ አሶሴሽን (Sasakawa Africa Association) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤርምያስ አባተ በበኩላቸው ሳሳካዋ አፍሪካ በኢትዮጵያ የግብርና ኤክስቴንሽን፣ የምግብ ዋስትና እና ዘላቂ የግብርና ስልጠናዎችን ሲሰጥ የቆየ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት መሆኑን ገልፀዋል፡: የግብርናው ዘርፍ የማይተካ ሚና ያለው ዘርፍ መሆኑን እና ዛሬ የምንሰራው ስራ ሁሉ ከተፈጥሮ ሀብት ጋር የሚጋጭና አጥፊ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባናል ብለዋል፡፡ ሳሳካዋ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመስራት የአርሶ አደራችን ህይወት ለመለወጥ የአቅማችን እገዛ እናደርጋለን ሲሉ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ኤክስቴንሽን መሪ ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ የኔነሽ ኢጉ እንደገለጹት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እጅግ ትልቅ ተቋም መሆኑን ጠቅሰው የዛሬው የመግባቢያ ሰነድም ከዚህ በፊት ሲሰሩ ከነበሩት ተግባራት በተሻለና በላቀ ደረጃ ውጤታማ ለማድረግ እንደ ግብርና ሚኒስቴር የሚጠበቅብንን ድጋፍ እንደምናደርግ ቃል እንገባለን ብለዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ በበኩላቸው ሰነዱ ዩኒቨርሲቲያችንና የሳሳካዋ አፍሪካ አሶሴሽን ሀገራችን ለምትጠብቀው የግብርና እድገት ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱና የኤክስቴንሽን ሰራተኞችን ትምህርት ከፍ በማድረግ ግብርናውን እንዲደግፉ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
የግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ዳንኤል ታደሰ በሁለቱ ተቋማት የሚፈጠረው ትብብር በግብርና ልማት፣በእውቀት ሽግግር እና በአቅም ግንባታ ዘርፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ አስረድተዋል፡፡
በጋራ መግባቢያ ሰነዱ ፊርማ ላይ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ ተመራማሪዎች እና መምህራን ተገኝተዋል፡፡
───
ለልህቀት እንተጋለን!
የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ
ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም