25/06/2026
እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ፕሮግራሞች ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመረቀ፡፡
ሰኔ 18/2018 ዓ.ም፤እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ
ዩኒቨርሲቲው ለ7ኛ ጊዜ በመደበኛ እና ተከታታይ መርሃ-ግብሮች በቅድመ ምረቃ እና ድህረ- ምረቃ ያስተማረቸውን ተማሪዎች በድምቀት አስመርቋል፡፡
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው የአጠቃለይ ዘርፍ ዩኒቨርሲቲ በመሆን በአዋጁ የተሰጡትን ተልዕኮዎች ለማሳለጥ በሰባት ኮሌጆች፤ በሁለት ትምህርት ቤቶች እና በአንድ ኢንቲትዩት ተደራጅቶ ግብርና እና አረንጓዴ ልማትን፤ የህብረተሰብ ጤናን፤ ቱሪዝም እና ስራ ፈጠራን እንዲሁም የአገው ባህል፤ ቋንቋ እና ታሪክ የትኩረት መስኮቹ በማድረግ ልዩ ስትራተጂክ እቅድ በማዘጋጀት ወደ ትግባራ ምዕራፍ መሸጋገሩን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ጋርዳቸው አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው በ2018 የትምህርት ዘመን 14ሽ 470 ተማሪዎችን በ59 የቅድመ-ምረቃ ፕሮግራሞች፣ በ47 የ2ኛ ዲግሪ ፐሮግራሞች እና በ5 የ3ኛ ዲግሪ (PhD) ፕሮግራሞች በድምሩ በ110 ፕሮገራሞች በማስተማር በዚህ ዓመት ለ7ኛ ዙር 2 ሽ 903 ተማሪዎችን ማስመረቁን ተናግረው ከእነዚህ ውስጥ በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በአገውኛ ቋንቋ እና ስነ-ጹሁፍ የመጀመሪያ ድግሪ ፕሮግራም ያስተማራቸውን 150 ተማሪዎች ማስመረቁን ገልፀዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም በ2018 ዓ.ም የመጨረሻው ዓመት የመውጫ ፈተና ከተፈተኑ 53 ትምህረት ክፍሎች ውስጥ 43 ትምህርት ክፍሎች 50 ከመቶ በላይ ተማሪዎቻቸውን ያሳለፋ ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ 15 ትምህርት ክፍሎች ማለትም Computer Scince, Chemistry, Mathematics, Statistics, Medical Laboratory, Nursing, Pediatrics and Child Health Nursing, Psychiatry, Food Science and Post-harvest-technology, Economics, Soft ware engineering, Management, Geography and Environmental studies, Sociology, Teacher education and curriculum study ትምህርት ክፍሎች 100 ፐርሰንት ተማሪዎች ማለፋቸውን ገልጸዋል፡፡
የእለቱ ክብር እንግዳ የሆኑት ገጣሚ፣ ሀያሲ፣ ደራሲ እና ጸሀፈ-ተውኔት ጋሽ አያልነህ ሙላቱ ለተመራቂ ተማሪዎች ባስተላለፉት ቁልፍ መልዕክት ዘመናዊ የምንለውን ሥርዓተ ትምህርት የምንፈጥረው ከውጭ ካገኘነው ልምድ ብቻ ተመስርተን በመገልበጥ ሳይሆን ወደ አገራችን ተመልክተን፣ አገር በቀል ዕውቀታችንን መሰረት ስናደርግ በመሆኑ ይህንንም ሥርዓተ ትምህርት ለማስተካከል የእናንተ የዛሬ ተመራቂዎች የወደፊት ሚና ትልቅ ነው በማለት ተመራቂ ተማሪዎች ሥልጣኔን የሚናፍቁ ወጣት ምሁራን በልዩነት ውስጥ አንድ ሆኖ ያሳደጋቸውን ማኅበረሰብ ባሕሉን ሳይበርዙ እና ሳይከልሱ፣ አገር በቀል ዕውቀቱን ከሕብረተሰቡ ተቀብለው ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር፣ በአገር በቀል ዕውቀት ላይ ዘመናዊ ሥልጣኔን የሚገነቡ እንዲሆኑ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ተገኝተው ለተመራቂ ተሪዎች መልዕክት ያስተላለፉት የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል እና የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳደሪ ቴዎድሮስ እንዳለው በበኩላቸው "በራሱ ላይ የሚሰራ ትውልድ ሀገርን ይሠራል" ተመራቂዎችም ራሳቸው ላይ በመሥራት እና በየጊዜው አቅማቸውን በማሻሻል ለማኅበረሰቡ ስኬት እና እድገት እንዲሠሩ፤ ማኅበረሰባቸውን እና ሀገራቸውን በማገልገል ውለታ ከፋይ እንዲሆኑ፤ በቀጣይ ሕይወታቸው ራሳቸውን ከሁኔታዎች ጋር አላምደው በአመለካከት ራሳቸውን ገንብተው በሚሠማሩበ የሥራ መስክ ሀገራቸውን እና ማኅበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
መርሃ ግብሩ በታላቅ ድምቀት ሲጠናቀቅ የ7ኛው ዙር የ2018 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎች ዋንጫ ተሸላሚ 4.00 በማስመዝገብ እና ከወሰዳቸው 55 ኮርሶች (46A+ እና 9A ) በማምጣት የሶፍትዌር ምንድህስና ተማሪ አላምራው ዋጋው የሁለት ሜዳሊያ እና የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን ከየኮሌጆች ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂ ተማሪዎችም የሜዲሊያ እና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት ለሙዚቃዋ ንግስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) የክብር ዶክትሬት ማበረክቱ የሚታወስ ሲሆን በዚህ ዓመትም ለዩኒቨርቲው እና ለሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለነበራቸው ጋሽ አያልነህ ሙላቱ አበጀ እና አባ ያዘው ዘለቀ ደስታ የምስጋና እና የእውቅና ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች፣ የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ከፍተኛ አመራሮች ፣ መምህራን፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የተማሪ ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡
ያለህን እምቅ አቅም ለይተህ ተጠቀም!