07/05/2025
የደጃዝማች ኩምሳ ሞረዳ ቤተ መንግስት የጥገናና የመልሶ ማልማት ስራ የውል ስምምነት ተደረገ
| ኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የደጃዝማች ኩምሳ ሞረዳ ቤተመንግስት የጥገናና የመልሶ ማልማት ስራ ለማከናወን ከቢዋይ ኤም ቲ ኮንትራክተር ጋር የውል ስምምነት ተፈራረመ ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በውል ስምምነቱ ላይ እንደገለፁት ቤተ መንግሥቱ ጥንታዊና ታሪካዊ መሆኑን ጠቅሰው ለረዥም ዓመታት እድሳት ሳይደረግለት ፣ በቱሪዝሙ ዘርፍ አገልግሎት ሳይሰጥ መቆየቱ አብራርተዋል ። ቅርሱ ከጥንት የኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የተያያዙ ስፍራዎችን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ከተመረጡ ስፍራዎች አንዱ መሆኑን ፣ጥገናው ቅርሱ የነበረውን አሻራና ይዘት በጠበቀ መልኩ የቅርስ ጥገና መርሆዎችን በተከተለ መንገድ በጥንቃቄ መከናወን እንዳለበት የጥገና ስራው በተያዘለት የሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ጥራቱን ጠብቆ መጠገንና ለሃገር ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መሆን እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡
እንዲሁም በውል ስምምነቱ ላይ መልእክታቸውን ያስተላለፉት ክብርት ወ/ሮ ህይወት ኃይሉ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ይህ የጥገና ስራ ቤተመንግስቱ ያለበትን የጥገና ችግር የሚፈታና ኮንትራክተሩ የተሳካ ስራ የሚያሳይበት እንደሚሆን ተመኝተው የቤተመንግስቱ እንዲሁም የምድረ ግቢው ጥገና በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለሀገራችን ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡
አቶ በዛብህ መለሰ የቢዋይ ኤም ቲዋና ስራ አስኪያጅ ይህን ታሪካዊ ቤተመንግስት ጥገና ለማድረግ ጨረታ በማሸነፋቸው መደሰታቸውን ገልጸው ስራውን በተፈለገው ጊዜና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ አከናውነው እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ደጃዝማች ኩምሳ ሞረዳ በከሬ ከ1881ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1916 ዓ.ም. ድረስ የቀድሞ ወለጋ ጠቅላይ ግዛትን ያስተዳድሩ ነበር ፡፡ ንጉሡ ቤተመንግስታቸውን የመሠረቱት 1830 ዓ.ም. ሲሆን ይህ አስደናቂ ቤተመንግስት ያረፈበት ቦታ ስፋቱ 2.5 ሄክታር የሚያካልል ነው፡፡ በቅጥር ግቢው ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ተደርገው የተገነቡ የተለያዩ ቤቶች ሲኖሩ በአጠቃላይ ቅጥር ግቢው አምስት በሮች አሉት፡፡
ይህ ቤተ መንግስት ከአዲስ አበባ በስተ-ምዕራብ በኩል 319 ኪሎ ሜትር ርቀት ነቀምቴ ከተማ ነው የሚገኘው፡፡ ይህም ከከተማዋ መሃል መነሻ ሆኖ በስተ-ምዕራብ በኩል 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከፍ ባለ ውብና ማራኪ ሥፍራ ተንጣሎ ይታያል፡፡
(ኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን)