26/09/2026
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት 11 አዳዲስ የሥልጠና ዘርፎችን ጨምሮ ምዝገባ ጀመረ
| የኢንስቲትዩቱትን መስፈርት የሚያሟሉ እና የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ላመጡ የመደበኛ ተማሪዎች ምዝገባ እስከ መስከረም 25/2019 ዓ.ም ድረስ ይቆያል ተብሏል፤
የፌዴራል የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት የዘመኑንና የወደፊቱን የገበያ ፍላጎት ያማከሉ ናቸው ያላቸውን አዳዲስ የሥልጠና መስኮችን በማካተት የተማሪዎች ምዝገባ እያከናወነ እንደሚገኝ ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ እነዚህን ተጨማሪ የስልጠና መስኮች ያስተዋወቀው ከመስከረም 14 ቀን 2019 ዓም ጀምሮ ክፍት የሚሆን የመረጃ ሳምንትን ይፋ ባደረገበት መርሃ ግብር ላይ ነው።
ኢንስቲትዩቱ ከ15 ዓመታት በላይ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ብቸኛው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሆኖ ሲሠራ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅትም፦
· በመጀመሪያ ዲግሪ (ደረጃ 6) 29 የትምህርት ፕሮግራሞች፣
· በሁለተኛ ዲግሪ (ደረጃ 7) 23 የትምህርት ፕሮግራሞች፣
· በሦስተኛ ዲግሪ (ደረጃ 8/ፒኤች.ዲ) 2 የትምህርት ፕሮግራሞች
በማካሄድ ላይ ይገኛል።
በተጨማሪም በ2018 ዓ.ም. ከዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ የክህሎት ፍላጎት ጋር የተጣጣሙ 11 አዳዲስ የሥልጠና መስኮችን ለማስተዋወቅና ለማስጀመር ሥራ መጀመሩ ተገልጿል። እነዚህም፦
- ባዮሜዲካል ቴክኖሎጂ፣
- የሳይበር ደህንነት፣
- አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)፣
- ኢንተለጀንት ሮቦቲክስ፣
- ፕላስቲክ ቴክኖሎጂ
- ሆርቲካልቸር
- ኢንቴሪየር ዲዛይን እና ፊኒሺንግ
- ሌዘር ፕሮዳክት
- በTVET ሊደርሺፕ እና ማኔጅመንት
- በማኑፋክቸሪንግ
- ፋሽን ዲዛይን እና በአዳዲስ ኢነርጂ ተሽከርካሪዎች ቴክኖሎጂ ዘርፍ የፈጠራና የወደፊት የሥልጠና መስኮች (Emerging Skills) ተቀርጸው ወደ ተግባር መግባታቸው ተገልጿል።
ሥልጠናው 50 በመቶ የንድፈ-ሀሳብ እና 50 በመቶ የተግባር ልምምድ እንዲሆን በተሟሉ ወርክሾፖች የተደገፈ ነው የተባለ ሲሆን ተቋሙ በ16 ሳተላይት ካምፓሶችና በ2 ማዕከላት አማካኝነት ከ 10 ሺ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሰልጠን ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል።
ኢንስቲትዩቱ ከቻይና እና አልጄሪያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጥምረት የዲግሪ ፕሮግራሞችን ከመስጠት ባሻገር፣ በየዓመቱ ከ300 በላይ ለሚሆኑ የደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ሌሎች የጎረቤት ሀገራት ዜጎች ነፃ የሥልጠና ዕድል እየሰጠ መሆኑን አሳውቋል።
የተቋሙን መስፈርት የሚያሟሉ የመደበኛ ተማሪዎች ምዝገባ እስከ መስከረም 25/2019 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ይፋ አድርጓል።